November 3, 2023
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እና የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከትምህርት ጋር የተያያዙ የማስታወቂያ ስርጭቶችን ህጋዊነትን በጋራ ለማስጠበቅ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ማስታወቂያዎች ህጋዊነት በቅንጅት መስራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ሰነዱን የፈረሙት የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ እድሪስ ናቸው፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ተዘጋጅተው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የትምህርት ተቋማት ማስታወቂያዎች ህጋዊነታቸውን እና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያግዝ እንደሆነ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ህዝቡን የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎችን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነት ያህል፡- “ሙሉ እውቅና ያለው” በሚል ማስታወቂያ ማስነገር ትክክል አይደለም፤ “ሙሉ እውቅና አለኝ” ብሎ ራሱን የሚያስተዋውቅ ተቋም “የሌላኛው ተቋም የእውቅና ፈቃድ ሙሉ አይደለም” የሚል ትርጉም ይኖረዋል፤ የእውቅና ሙሉ የእውና ፈቃድ ተብሎ የሚሰጥ ፈቃድ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ህዝብን ያሳስታል፤ ለአንድ ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ወይም በኢኮኖሚክስ የእውቅና ተሰጥቶታል ካለ፤ የተሰጠው በየትኛው ካምስ እንደሆነ መግለጽን ይፈልጋል፣ የምንሰጠው የእውቅና ፈቃድ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ ነው፤ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማስታወቂያ አዘጋጅተው የሚያሰራጩ የማስታወቂያና የሚዲያ ድርጅቶች ይህን መሰረት አድርገው መስራት አለባቸው፤ ከዚህ አንጻር ሁለቱ ባለስልጣን መ/ቤቶች የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ የትምህርት ማስታወቂያዎች ህጋዊነታቸው ተጠብቆ በጥራት እንዲሰራጩ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ገልጸዋል።
እንዲሁም የማስታወቂያና የሚዲያ አካላት የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማስታወቂያ አዘጋጅተው ከማሰራጨታቸው በፊት የሚከተሉትን መመሪያዎች መሰረት አድርገው እንዲሰሩ አንስተዋል፤ እነዚህም
- በኢትዮጵያ ውስጥ በበይነ-መረብ የትምህርት አሰጣጥ የእውቅና ፈቃድ መመሪያ መሰረት በባለስልጣኑ ከተፈቀደላቸው ተቋማት ውጪ ተማሪ ተቀብለው ማስተማር ስለማይችሉ የማስታወቂያ እና የሚዲያ አካላት የእውቅና ፈቃዳቸውን አይተው በማረጋገጥ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡
- ድንበር ተሻጋሪ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ የእውቅና ፈቃድ ተሰጥቷቸው ማስተማር የሚችሉት በድህረ-ምረቃ የትምህርት መስክ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ዲግሪ ማስታወቂያ ማስነገር አይችሉም፡፡
- ከህሙማን ጋር ግንኙነት ያላቸው የጤና ስልጠናዎች በቅዳሜ፣ በእሁድ እና በማታው መርሃ-ግብር አሰልጥነው ማስመረቅ አይችሉም፤ ስለዚህ ማስታወቂያ ማስነገር የሚችሉት በመደበኛ በሚል ብቻ ነው፡፡
- የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ሳይፈቀድላቸው ከግል ድርጅቶች ጋር የትብብር ስልጠና መስጠት የተከለከለ ስለሆነ ከማንኛውም ድርጅት ጋር በመተባበር የሚሰጥ ትምህርት እና ስልጠና በሚል ማስታወቂያ ማስነገር አይችሉም፡፡
- የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በርቀት ትምህርት መስጠት ከፈለጉ ከትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የእውቅና ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፤ እንዲሁም በራሳቸው ፍላጎት ካሉበት አካባቢ ውጪ ርቀው የርቀት ትምህርት ቅርንጫፍ ከፍተው ማስተማር አይችሉም፡፡ ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረኑ ማስታወቂያዎችን ማስነገር ስለማይችሉ የማስታወቂያ ድርጅቶች በቅድሚያ ለዩኒቨርሲቲዎች በርቀት ትምህርት የተሰጣቸው የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤያቸውን ሳያዩ የማስታወቂያ ስራውን ማስተናገድ የለባቸውም፡፡
- የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በርቀት ትምህርት መስጠት ከፈለጉ ከትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የእውቅና ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፤ እንዲሁም በራሳቸው ፍላጎት ካሉበት አካባቢ ውጪ ርቀው የርቀት ትምህርት ቅርንጫፍ ከፍተው ማስተማር አይችሉም፡፡ ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረኑ ማስታወቂያዎችን ማስነገር ስለማይችሉ የማስታወቂያ ድርጅቶች በቅድሚያ ለዩኒቨርሲቲዎች በርቀት ትምህርት የተሰጣቸው የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤያቸውን ሳያዩ የማስታወቂያ ስራውን ማስተናገድ የለባቸውም፡፡
- የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የደረጃ ስያሜን በተመለከተ ማንኛውም የግል ተቋም ራሱን ማስተዋወቅ የሚችለው በደረጃ ስያሜ መመሪያው መሰረት ተገምግሞ በተሰጣው የደረጃ ስያሜ መሰረት ብቻ ነው፤ በባለስልጣኑ የተሰጣቸው የደረጃ ስያሜ እያለ በራሳቸው ተነሳሽነት ባልተፈቀደላቸው የደረጃ ስያሜ ራሳቸውን ማስተዋወቅ አይችሉም፤ በመሆኑም ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ አካላት የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤያቸው ላይ የሰፈረውን የደረጃ ስያሜ ብቻ መጠቀም አለባቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የተፈቀደላቸው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል የደረጃ ስያሜ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ማስታወቂያ ማስነገር የተከለከለ ነው፤ እንዲሁም ኮሌጅ የሚል የደረጃ ስያሜ ያላቸው ራሳቸውን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ብለው ማስታወቂያ ማስነገር እንደማይችሉ ዶክተር አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡
ዶክተር አንዱዓለም አክለውም የትምህረት ማስታወቂያዎችን የሚያሰራጩ የሚዲያ ድርጅቶች የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የወጡ ህግና መመሪያዎችን መሰረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል፤ ህዝባችንን የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎች እና መረጃዎች መሰራጨት የለባቸውም ብለዋል፡፡ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትም በተሰጣቸው የእውቅና ፈቃድ ላይ ብቻ ተመስርተው ራሳቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
አዲስ የተቋቋመው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ባሻገር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎችን እና የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፎች ድረስ የሚወርድ ስልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል ብለዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባለስልጣኑ ተግባር፣ ስልጣንና አደረጃጀት ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉትን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየዳበረ መሆኑን ገልጸው ይህም የትምህርት ጉዳይ የሀገር ተረካቢ ትውልድን የመቅረጽ ጉዳይ በመሆኑ ሚዲያዎችም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡