በአንድ ወር ጊዜ የተማሪዎችን መረጃ ወደ ሲስተም ማስገባት አለበት

ማንኛውም ተቋም ተማሪዎችን በመዘገበ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተማሪዎቹን መረጃ ወደ ሲስተሙ ማስገባት አለበት፤ ሲያስመርቅ ደግሞ የተቋሙ ሴኔት ባጸደቀ በማግስቱ የተመራቂዎቹን ማስረጃ በሲስተሙ መግባት ይኖርበታል፡፡
እየተበራከተ የመጣውን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይከላከላል ተብሎለት ከዓመታት በፊት በትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የተዘጋጀው ቴክኖሎጂ ከምን ደረሰ? በሚለው ጉዳይ ላይ ሀገሬ ቴሌቪዥን ከኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አድማሴ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትምህርት ማስረጃን ለመከላከል እንዲያስችል ህጋዊነቱን እና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የሚጠይቀው ሂደት ረጅም ስለነበር አድካሚ ሆኖ ቆይቷል፤ ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ያሁኑ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ተቋማት እና ግለሰቦች ሰራተኞችን ለመቅጠር በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳይታለሉ መዘርጋቴን እወቁልኝ ማለቱ የሚታወስ ነው፤ ተቋሙ ቴክኖሎጂውን መዘርጋቱ መልካም ጅምር ቢሆንም ወደ ሲስተሙ የገቡ ተማሪዎች ቁጥር ግን ዝቅተኛ ነው፤ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሲስተሙ 1.1 ሚሊዮን ዜጎች ብቻ በሲስተሙ ተመዝግበዋል፤ የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመከላከል የተጀመረው እንቅስቃሴ ከምን ደረሰ? ሲል ከሀገሬ ቴሌቪዥን ለተነሳላቸው ጥያቄ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱዓለም አድማሴን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እንደተናገሩት ተቋማት የተቀበሏቸውን ተማሪዎች በሲስተም ውስጥ ያስገባሉ፤ ማንኛውም ተቋም ተማሪዎችን በመዘገበ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተማሪዎቹን መረጃ ወደ ሲስተሙ ማስገባት አለበት፤ ሲያስመርቅ ደግሞ ሴኔት ስላላቸው ሴኔቱ ባጸደቀ በማግስቱ የተማሪዎቹ ማስረጃ በሲስተሙ መግባት ይኖርበታል፤ ይህ በሚደረግበት ጊዜ የመግቢያ መስፈርቱ እና ሌሎች መሟላት ያለባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ካልተሟሉ ሲስተሙ አይቀበልም፤ እንደገና ፊልተር ይደረግና ትክክለኛ የሆኑትንና ያልሆኑትን ይለያል፤ ከዚያም ኢንኮደሮቹ ኤዲት ያደርጉታል፤ የትኛውንም ማስረጃ ከተፈለገ በማንኛውም ጊዜ ከሲስተሙ ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ ባልተፈቀደ ካምፓስና የትምህርት መስክ አስመርቆ በሲስተሙ ማስገባት አይችልም፤ ካስገባም ይያዛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አንድ ተቋም የመዘገባቸውን ተማሪዎችን እና የተመራቂዎችን መረጃ ወደ ሲስተሙ ሲያስገባ ከባለስልኑ ፈቃድ ያገኘበትን ብቻ ነው የሚያስገባው፤ ሌሎቹ ተማሪዎች ግን የትምህርት ማስረጃቸውን ቢጠይቁ ማንም ሊሰጣቸው የሚችል አካል የለም፤ ስለዚህ ትልቁ ተግዳሮት ባለፉት 20 አመታት ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ተቀብሏቸው ያስመረቋቸው ዴታ በእጃቸው አለ፤ በተለይ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ተቋማት፤ እንዲህ አይነት ተቋማት ይህን መረጃ ዛሬ ቢያስገቡ እኛ ነገ ጠዋት ገብተን ማየታችን አይቀርም፤ ሲታይ ባልተፈቀደ ካምፓስ እና የትምህርት መስክ የተማረ፣ መስፈርት ሳያሟላ ተመዝግቦ የተማረውን ወደ ሲስተሙ ማስገባቱ ከተረጋገጠ ክስ ይመሰረትበታል ብለዋል፡፡ ሲስተሙም አዲስ በመሆኑ ምን ያህል ሊሸከም እንደሚችል እና ሌሎች ክፍተቶችም ካሉ በተግባር እየፈተሸነው እያሻሻልነው የምንሄድበት ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ድርጅቶች የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመከላከል ከመቅጠራቸው በፊት የሚቀጥሩትን ሰራተኛ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ሳይቀጥሩ የትምህርት ማስረጃቸው ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማጣራት ወደ ባለሥልጣን መ/ቤታችን ቢልኩ በደስታ እናጣራላቸዋለን ሲሉ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡