በማስታወቂያ ስርጭቶች ላይ ጠንካራ የክትትል ስራ ይሰራል

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እና የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከትምህርት ጋር የተያያዙ የማስታወቂያ ስርጭቶችን ህጋዊነትን በጋራ ለማስጠበቅ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ማስታወቂያዎች ህጋዊነት በቅንጅት መስራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ሰነዱን የፈረሙት የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ እድሪስ ናቸው፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ተዘጋጅተው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የትምህርት ተቋማት ማስታወቂያዎች ህጋዊነታቸውን እና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያግዝ እንደሆነ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ህዝቡን የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎችን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነት ያህል፡- “ሙሉ እውቅና ያለው” በሚል ማስታወቂያ ማስነገር ትክክል አይደለም፤ “ሙሉ እውቅና አለኝ” ብሎ ራሱን የሚያስተዋውቅ ተቋም “የሌላኛው ተቋም የእውቅና ፈቃድ ሙሉ አይደለም” የሚል ትርጉም ይኖረዋል፤ የእውቅና ሙሉ የእውና ፈቃድ ተብሎ የሚሰጥ ፈቃድ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ህዝብን ያሳስታል፤ ለአንድ ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ወይም በኢኮኖሚክስ የእውቅና ተሰጥቶታል ካለ፤ የተሰጠው በየትኛው ካምስ እንደሆነ መግለጽን ይፈልጋል፣ የምንሰጠው የእውቅና ፈቃድ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ ነው፤ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማስታወቂያ አዘጋጅተው የሚያሰራጩ የማስታወቂያና የሚዲያ ድርጅቶች ይህን መሰረት አድርገው መስራት አለባቸው፤ ከዚህ አንጻር ሁለቱ ባለስልጣን መ/ቤቶች የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ የትምህርት ማስታወቂያዎች ህጋዊነታቸው ተጠብቆ በጥራት እንዲሰራጩ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ገልጸዋል።

እንዲሁም የማስታወቂያና የሚዲያ አካላት የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማስታወቂያ አዘጋጅተው ከማሰራጨታቸው በፊት የሚከተሉትን መመሪያዎች መሰረት አድርገው እንዲሰሩ አንስተዋል፤ እነዚህም

ዶክተር አንዱዓለም አክለውም የትምህረት ማስታወቂያዎችን የሚያሰራጩ የሚዲያ ድርጅቶች የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የወጡ ህግና መመሪያዎችን መሰረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል፤ ህዝባችንን የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎች እና መረጃዎች መሰራጨት የለባቸውም ብለዋል፡፡ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትም በተሰጣቸው የእውቅና ፈቃድ ላይ ብቻ ተመስርተው ራሳቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ አዲስ የተቋቋመው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ባሻገር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎችን እና የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፎች ድረስ የሚወርድ ስልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል ብለዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባለስልጣኑ ተግባር፣ ስልጣንና አደረጃጀት ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉትን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየዳበረ መሆኑን ገልጸው ይህም የትምህርት ጉዳይ የሀገር ተረካቢ ትውልድን የመቅረጽ ጉዳይ በመሆኑ ሚዲያዎችም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡