November 3, 2023
ሕጋዊ ያልሆኑ የትምሕርት ተቋማት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን የትምሕርትና ሥልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ አዲስ አበባ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የትምሕርት ተቋማት መስፋፋት የትምሕርት ጥራት ጥያቄ ዉስጥ እዲወድቅ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነዉ ሲሉ የኢፌዴሪ የትምሕርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ.ር) አስታወቁ፡፡
በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደረገ የመጀመሪያ ዙር የተቋማት ፍተሻ ከ147 ተቋማት ዉስጥ በ 106 የትምሕርት ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡ በሁለተኛ ዙር በክልሎች ባሉ የትምሕርት ተቋማት በተደረገ ፍተሻ ደግሞ በ 95 ተቋማት ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡
ትዉልድን በመቅረጽ እና ሀገርን በመገንባት ሂደት የትምሕርትን ሚና የሚያክለዉ እንደሌለ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሂደት የትምሕርት ሚና ትርጉም የሚኖረዉ ግን ጥራቱን የጠበቀ ከኾነ ብቻ ነዉ ብለዋል፡፡
ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢፌዴሪ የትምሕርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ፤ አሁን ላይ የትምሕርት ጥራት በኢትዮጵያ ጥያቄ ዉስጥ የገባበትን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኀላፊነት የማይሰማቸዉ እና ትርፍን ብቻ ዒላማ ያደረጉ ሕገወጥ የግል የትምሕርት ተቋማት መስፋፋት ምክንያት እንደኾኑ ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የትምሕርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየወሰዳቸዉ ካሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሕገ ወጥ የትምሕርት ተቋማትን መቆጣጠር አንዱ ተግባር እንደኾነ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ፈቃድ ሳያገኙ ትዉልድን እያቀጨጩ እና የምስኪኑን አርሶ አደር ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጎዱ ያሉ ሕገ ወጥ የግል ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ለመቆጣጠር በሚደረገዉ ሂደት ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾን አስገንዝብዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ስለተቋማት ሕጋዊነት በ9799 ነጻ የስልክ ቁጥር ደዉሎ ማረጋገጥ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡